Tesfahiwot

[አባ ገብረ ኢየሱስ]
ቅድስት ቤተ ክርክስቲያን የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የዘወትር ትምህርት ብቻ ሳይሆን የሕይወት ምግብ የሕይወት መጠጥ ሁኖ የሚኖርባት የእግዚአብሔር ማኅደሩ ናት፡፡ የእያንዳንዱ አገልግሎት ማዕከልም በክርስቶስ የተፈጸመልን ነገረ ድኅነት ነው ” ይህን ሁሉ ያደረገው ግን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሳው ሥጋና ነፍስ ቃል ከሥጋ ጋር ተዋህዶ ነው ፡፡ ” ጻእረ ዘሞት ፈትሐ ኢኮነ ባሕቲቶ ከዊኖ ሰብአ ዘእመንፈስ ቅዱስ ” =የሞትን ጻዕር(ፍዳ) አሰናበተው ይኸውም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ቃል ሥጋን ተዋሕዶ ነው እንጂ ቃል ብቻውን አይደለም ” እንዲል
በዚህ የቤዛነት /የማዳን ሥራ እግዚአብሔር ንጽሕት ድንግል ማርያምን ምክንያት አድርጓል ቃል ዓለምን ለማዳን መከራ የተቀበለው ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ ነውና “ቤዛዊተ ኩሉ ዓለም ” ትባላለች [ ]
ወዲኽም ልዑል እግዚአብሔር ለእመቤታችን በሰጣት በኪዳነ ምሕረት የቤዛነት ጸጋ አላት ፡፡ እንኳንስ ወላዲተ ቃል ድንግል ማርያምን እግዚአብሔር እነ ሙሴን ለወገኖቻቸው ቤዛ አድርጓቸዋል ፡፡
“ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው።”(ሐዋ 7፥35 )
ነገር ግን
✍ የቤተክርስቲያን የነገረ ድኅነት ትምህርት ከዚህ በፊት ያልተነገረ “አሁን በእገሌ” የሚሰበክ አዲስ ትምህርት አድርጎ ማቅረብ አይገባም ፡፡
✍ በነገረ ድኅነት ትምህርት ስም ኦርቶዶክሳዊ(አባታዊ) ላሕይ የተለየው ፣ ቀደምት አበው ያልተናገሩት ሌላ እንግዳ አነጋገር ማምጣት (ዕሩቅ ትምህርት) ማንንም አያንጽም ፡፡
✍ የሰዎችን ፍላጎት ወደ እግዚአብሔር ሀሳብ [ትምህርት ፈቃድ ] ማምጣት ነው እንጂ °°የሰዎችን ፍላጎት ተከትሎ /ለሰዎች ደስ ይበል ተብሎ የሚሰጥ ትምህርት ቤተ ክርስቲያናዊነት ይርቀዋል ፡፡
✍ በነገረ ማርያም ትምህርት ላይ ተቃርኖ የተጫነው የድፍረት አነጋገር የጤነኛነት መገለጫ አይደለም
✍ በሰሙነ ሕማማት ከመደበኛው አገልግሎት ተለይቶ ወደ አዳራሽ ትምህርት መሔድና ያልጠራ ትምህርት አስተምሮ አጀንዳ መፍጠር ተገቢነት ይጎድለዋል ፡፡ አይገባምም ፡፡
✍ በተረጋጋ ስሜት ሁኖ ማስተማርና መማር ይገባል ስህተቶችንም በትሕትና በጊዜው ማረም/ማስተካከል ካልተቻለ <ለዚህ ሰው ከበፊቱ ይልቅ የሗለኛው የከፋ ይሆንበታል >
” ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ “
እግዚአብሔር ከመረጣቸው ጋር ባደረገው ኪዳኑ ይጠብቀን

              © አባ ገብረ ኢየሱስ

Leave A Comment

error: