Tesfahiwot

ክርስቶስ አምላክነ ዘመጽአ ወሐመ በእንቲአነ በሕማማቲሁ ቤዘወነ (በመከራው ዋጀን)
ሕማማት ክርስቶስ ያገኘው መከራ ስቃያት ናቸው። ሕማሙ የራስ ፍልጠት የሆድ ቁርጠት አይደለም። መገረፍ፣ መደብደብ፣ በጥፊ መመታት፣ መረገጥ፣ መሰደብ፣ ምራቅ መተፋት፣ መገፍተር የመሳሰለው ነው። “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው” ኢሳ.53:4
ሕማሙን ማሰብ ድኅነታችን ነው። የክርስቶስ የኾኑ ሰዎች የሚታወቁት በክርስቶስ ሕማም ነው። “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን” 2 ቆሮ.4:20
ክርስቶስን መውደዳችን በዚኽ ሕሊና ጨክነን እንድንኖር፣ መከራ እንድንቀበል ያደርገናል። ሕማሙን የምናስበው መከራ እየተቀበልን ነው። የመዳን ምልክት የፍቅር ምልክት ነው። ለእኛ ያደረገውን ማሰብ ነው።
የማይነጥፍ ደስታ ያለው የክርስቶስን ሞትና መከራ ማሰብ ውስጥ ነው። ደሙ ሲፈስ ለእኛ ደስታ ሕይወት ፈለቀልን። ከእግዚአብሔር የማትለይ ፍቅር ይኽንን ማሰብ ነው።
♦የክርስቶስ ሞት ፊት ለፊቱ የሚታየው ሰው አይበድልም። ቢበድልም ቶሎ ይመለሳል። ሥጋውን ገቶ ይይዛል።
♦የክርስቶስን መከራ ማሰብ በመከራ ጊዜ ያስታግሳል። እርሱ ሳይገባው መከራ ተቀብሏል እኔ ግን መከራው የሚገባኝ ነኝ ሲል ትዕግስትን ይይዛል። “ፍቅር በሁሉ ይታገሳል” 2 ቆሮ.15:
♦ የክርስቶስን ፍቅር ያየ ሰው ሌላውን ይታገሳል። ጠላት እንወዳለን። ሰው ሁኖ ለእኛ የተደረገውን ውለታ ማሰብ ይገባል። እግዚአብሔር ምን እንዳደረገልን ስናውቅ እንወደዋለን። ሕማሙ ውለታውን እናስባለን።
ሰው ይሆን ዘንድ ግድ ያለው ምንድነው? ጲላጦስ ይዘባበትበት ዘንድስ ግድ ያለው ምንድነው? በመስቀል ይሰቀልስ ዘንድ ያተጋው ምንድነው፣ በመቃብር ሦስት መዓልትና ሌሊት ያድር ዘንድ ያተጋው ምንድነው? በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አደርጎ እንዲነሣ ያተጋው ምንድነው? ጠፍተን ሙተን የነበርነውን እኛን ለማንሣት ነው። (እለ እስክንድሮስ ሃይማኖተ አበው)
በሁሉ የሚፈርደውን ጌታ ፈረዱበት፣ ሰውን ሁሉ ከኃጢአት ማሰሪያ የሚፈታውን እርሱን በገመድ አሰሩት። “ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፦ አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው” ማር.2:5
ዓለምን በመሐል እጁ እንደ ጽንሐሕ አንጠልጥሎ፣ እንደ ወርቅ አንከብሎ የያዘውን እርሱን በወታደሮች ተያዘ። ይኽንን እያሰብን ራሳችንን እንገስጻለን። በራሳችን ላይ እንፈርዳለን። “ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን” 1. ቆሮ.11:31
“ሰውነቱን ሊያገኝ የሚወድ ይጣላት” በመስቀል ላይ ራሱን ዘር አድርጎ ይጣል ማለት ነው። በመከራ መስቀል ይጣላት ከብራ ያገኛታል፣ ሰውነቱን በመከራ የጣላት ከብራ ያገኛታል ማለት ነው።
ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚያድለውን ጌታ ከርቤ ሐሞትን መራራ አጠጡት። ምእመናን አፋቸውን እስኪመራቸው ይጾማሉ። ሕማማቱን ማሰብ መዳን ነው። “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” ገላ.2:16 ለሥጋ ፈቃድ ነጻነት አለመስጠት ነው።
♦በዚኽ ሁሉ ሕማሙ እኛን ቤዛ ሆነን። “ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” 1 ቆሮ.6:19
[ንዋይ ካሳሁን]

Leave A Comment

error: